የባህር ዳር ከተማን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ 10 በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ዘመናዊ አውቶቡሶች ተገዝተው ርክክብ ተፈጸመ።
የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ አውቶቡሶቹ ከቢኬጂ ግሩፕ የተረከቡ ሲሆን፣ በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እነዚህ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ባሶች ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ ከመሆናቸው ባለፈ፣ የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመንና ለነዋሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ መሆኑን አቶ ጎሹ አብራርተዋል።
በርክክብ ሥነስርዓቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የከተማ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
አውቶቡሶቹ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩና በቀጣይም ተጨማሪ የትራንስፖርት ግብዓቶችን ለማሟላት እንደሚሠራ ተመላክቷል።
በሙሉጌታ ምህረት
